ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 21:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።

2. ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።

3. ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል።

4. እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”

5. በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለ።

6. እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ።

7. ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።

8. ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኵሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”

9. ሰባቱ የመጨረሻ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” አለኝ።

10. በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወስዶኝ፣ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።

11. እርሷም በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 21