ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 18:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!የአጋንንት መኖሪያ፣የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች።

3. ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመንዝረዋል፤የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይልየተነሣ በልጽገዋል።”

4. ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤“ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ከእርሷ ውጡ፤

5. ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሮአልና፤እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሶአል።

6. በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።

7. ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤“እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤መበለትም አይደለሁም፤ ከቶምአላዝንም፤”

8. ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለ ሆነ፣በእሳት ትቃጠላለች።

9. “ከእርሷ ጋር ያመነዘሩና በምቾት የኖሩ የምድር ነገሥታት፣ እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም።

10. ሥቃይዋንም በመፍራት በሩቅ ቆመው እንዲህ ይላሉ፤“አንቺ ታላቂቱ ከተማ ወዮልሽ! ወዮልሽ!”አንቺ ባቢሎን ብርቱዪቱ ከተማ፣ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥቶአል።”

11. “ጭነታቸውን ከእንግዲህ የሚገዛ ስለሌለ፣ የምድር ነጋዴዎችም ስለ እርሷ ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉ፤

12. ጭነቱም፦ ወርቅ፣ ብር፣ የከበረ ድንጋይ፣ ዕንቍ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ፣ ሐምራዊ ልብስ፣ ሐር ልብስ፣ ቀይ ልብስ፣ መልካም ሽታ ያለው ዕንጨት ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ከውድ ዕንጨት፣ ከናስ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ዕቃ ሁሉ፣

13. ቀረፋ፣ ቅመም፣ ከርቤ፣ ቅባት፣ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የተሰለቀ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገሎች፣ እንዲሁም ባሮችና የሰዎች ነፍሶች ነው።

14. እነርሱም፣ ‘የተመኘሽው ፍሬ ከአንቺ ርቆአል፤ ብልጽግናሽና ክብርሽ ሁሉ ጠፍቶአል፤ ዳግመኛም ተመልሶ አይመጣም” ይላሉ።

15. እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእርሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን ፈርተው በሩቅ ይቆማሉ፤ እነርሱም ያለቅሳሉ፤ ያዝናሉም፤

16. ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ ይላሉ፤“ቀጭን የተልባ እግር፣ ሐምራዊና ቀይ ልብስ የለበሰች፣በወርቅ፣ በከበረ ድንጋይና በዕንቍም ያጌጠች፣ታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት!

17. ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።”“የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሮአቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ።

18. እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 18