ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በአውሬው ላይ የተቀመጠችው ሴት

1. ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ እንዲህ አለኝ፤ “ና፤ በብዙ ውሆች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን አመንዝራ ፍርድ አሳይሃለሁ።

2. የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመነዘሩ፤ የምድር ነዋሪዎችም በዝሙቷ የወይን ጠጅ ሰከሩ።”

3. ቀጥሎም መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በዚያም አንዲት ሴት በስድብ ስሞች በተሞላ፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣ አየሁ።

4. ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ተጐናጽፋ ነበር፤ ደግሞም በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቆችም አጊጣ ነበር፤ በእጇም የሚያስጸይፍ ነገርና የዝሙቷ ርኵሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር።

5. በግምባሯም ላይ እንዲህ የሚል የምስጢር ስም ተጽፎ ነበር፤ታላቂቱ ባቢሎን፣የአመንዝሮችናየምድር ርኵሰቶች እናት።

6. ሴቲቱንም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት።ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅሁ።

7. ከዚያም መልአኩ እንዲህ አለኝ፤ የምትደነቀው ለምንድን ነው? የሴቲቱን፣ እርሷ የተቀመጠችበትንም፣ እንዲሁም ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እነግርሃለሁ።

8. ያየኸው አውሬ ቀደም ሲል ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ በኋላም ከጥልቁ ጒድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ የምድር ነዋሪዎች አውሬው ቀድሞ የነበረ፣ አሁን ግን የሌለ፣ በኋላም የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ።

9. “ይህም፣ ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የምትቀመጥባቸው ሰባት ተራሮች ናቸው፤

10. እነርሱም ደግሞ ሰባት ነገሥታት ናቸው። አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣ ግን ሊቈይ የሚገባው ለጥቂት ጊዜ ነው።

11. ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ስምንተኛው ንጉሥ ነው፤ እርሱም ከሰባቱ አንዱ ሲሆን ወደ ጥፋቱ ይሄዳል።

12. “ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ፣ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንዲነግሡ ሥልጣን ይቀበላሉ።

13. አንድ ሐሳብም አላቸው፤ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ፤

14. እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉ ግን ድል ይነሣቸዋል፤ ምክንያቱም እርሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው፤ ከእርሱ ጋር ያሉ የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም አብረው ድል ይነሣሉ።”

15. መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራዪቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሆች፦ ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ናቸው።

16. አውሬውና ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች አመንዝራዪቱን ይጠሏታል፤ ባዶዋንና ዕራቍቷን ያስቀሯታል። ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል።

17. የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ ዕቅዱን እንዲፈጽሙ፣ ደግሞም በአንድ ሐሳብ እንዲስ ማሙና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው እንዲሰጡ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነውና።

18. ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።