ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 14:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ።

2. ከሰማይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁት ድምፅ በገና ደርዳሪዎች እንደሚደረድሩት ዐይነት ነበረ።

3. እነርሱም በዙፋኑ ፊት፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ መዝሙር ዘመሩ። ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች በስተቀር መዝሙሩን ማንም ሊማረው አልቻለም።

4. እነዚህ ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱት ናቸው፤ ራሳቸውን በንጽሕና ጠብቀዋልና። በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው።

5. በአፋቸው ምንም ዐይነት ውሸት አልተገኘም፤ ነቀፋም የለባቸውም።

6. ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤

7. በታላቅ ድምፅም፣ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” አለ።

8. ሌላም ሁለተኛ መልአክ፣ “ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች ወደቀች!” እያለ ተከተለው።

9. ሦስተኛውም መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ማንም ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ፣ ምልክቱንም በግምባሩ ወይም በእጁ ላይ የሚቀበል ቢኖር፣

10. እርሱ ደግሞ ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት በቍጣው ጽዋ ውስጥ የተሞላውን የእግዚአብሔርን ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል። በቅዱሳን መላእክትና በበጉ ፊትም በእሳትና በዲን ይሠቃያል።

11. የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ ወይም የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።”

12. የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 14