ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሴቲቱና ዘንዶው

1. ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች አንዲት ሴት ታየች።

2. እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድ ስትል ምጥ ይዞአት ተጨንቃ ጮኸች።

3. ከዚያም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት አክሊል የደፋ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ።

4. ጅራቱ የከዋክብትን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ እርሷም በወለደች ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ዘንዶው ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ።

5. ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።

6. ሴቲቱም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳ ዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።

7. በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤

8. ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ።

9. ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

10. ከዚህ በኋላ ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤“አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልናመንግሥት፣የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቶአል።ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸውየነበረው፣የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።

11. እነርሱም በበጉ ደም፣በምስክርነታቸውም ቃል፣ድል ነሡት፤እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣ለነፍሳቸው አልሳሱም።

12. ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ደስ ይበላችሁ፤ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻእንደ ቀረው ስላወቀ፣በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።

13. ዘንዶው ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ፣ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።

14. ሴቲቱም በበረሓ ወደ ተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል ሁለት የታላቁ ንስር ክንፎች ተሰጣት፤ ይህም የሆነው በዚያ ከእባቡ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በክብካቤ እንድትኖር ነው።

15. እባቡም ሴቲቱ በጐርፍ ተጠራርጋ እንድትወሰድ፣ እንደ ወንዝ ያለ ውሃ ከአፉ ተፋ።

16. ምድር ግን ሴቲቱን ረዳቻት፤ አፏንም ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠች።

17. ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።