ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 1:10-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ከበስተ ኋላዬ ሰማሁ፤

11. ድምፁም፣ “የምታየውን በጥቅልል መጽሐፍ ጽፈህ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላድልፍያና በሎዶቅያ ወደሚገኙት ወደ ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ላክ” አለ።

12. እኔም የሚናገረኝን ድምፅ ለማየት ዞር አልሁ፤ ዞር ባልሁም ጊዜ ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ፤

13. በመቅረዞቹም መካከል “የሰው ልጅ የሚመስል” አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ የሚደርስ መጐናጸፊያ የለበሰ፣ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።

14. ራሱና ጠጒሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጒር፣ እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም የእሳት ነበልባል ይመስሉ ነበር።

15. እግሮቹ በእቶን እሳት የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ወራጅ ውሃ ድምፅ ነበረ።

16. በቀኝ እጁ ሰባት ከዋክብት ይዞ ነበር፤ ከአፉም በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ይወጣ ነበር፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሓይ ነበረ።

17. ባየሁት ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅሁ። እርሱም ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፤ “አትፍራ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤

18. እኔ ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ እነሆ አሁን ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦል መክፈቻም በእጄ ነው።

19. “ስለዚህ ያየኸውን፣ አሁን ያለውንና በኋላም የሚሆነውን ጻፍ።

20. በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምስጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 1