ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 9:17-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደህና ተጠብቀው ይቈያሉ።”

18. ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ ሹም ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው።

19. ኢየሱስም ተነሥቶ አብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

20. ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት ከኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ነካች።

21. እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር።

22. ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፤ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች።

23. ኢየሱስ ወደ ምኵራብ አለቃው ቤት እንደ ደረሰ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣

24. “ዞር በሉ፤ ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት።

25. ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ልጅቱም ተነሥታ ቆመች።

26. ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሰራጨ።

27. ኢየሱስም ከዚያ እንደሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረን” በማለት እየጮኹ ተከተሉት።

28. ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት።

29. ከዚያም ኢየሱስ ዐይናቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው።

30. ዐይናቸውም በራ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው።

31. እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 9