ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 24:7-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤

8. ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው።

9. “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።

10. በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም።

11. ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ።

12. ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤

13. እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።

14. ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።

15. “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተነገረው፣ ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል።

16. በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤

17. በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤

18. በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ።

19. ‘በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!

20. እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ፤

21. በዚያን ጊዜ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል።

22. ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።

23. በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤

24. ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ።

25. እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 24