ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 23:22-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. በሰማይ የማለም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

23. “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤

24. እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ።

25. “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ትወለውላላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ስስት ሞልቶባቸዋል።

26. አንተ ዕውር ፈሪሳዊ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል።

27. “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኵሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ!

28. እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው።

29. “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር እየገነባችሁ፣ የጻድቃንንም ሐውልት እያስጌጣችሁ፣

30. ‘በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁና።

31. በዚህም የነቢያት ገዳዮች ለነበሩት አባቶቻችሁ ልጆች መሆናችሁን በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።

32. እንግዲህ የአባቶቻችሁን ጅምር ተግባር ከፍጻሜ አድርሱ!

33. “እናንተ እባቦች፤ የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ?

34. ስለዚህ ነቢያትን፣ ጠቢባንንና መምህራንን እልክላችኋለሁ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹንም በምኵራቦቻችሁ ትገርፏቸዋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዷቸዋላችሁ።

35. ስለዚህ፣ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው ንጹሕ ደም ሁሉ እናንተ ተጠያቂዎች ናችሁ።

36. እውነት እላችኋለሁ፤ ላለፈው ነገር ሁሉ ይህ ትውልድ ይጠየቅበታል።

37. “አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፤

38. እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!

39. እላችኋለሁና፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስከምትሉ ድረስ ዳግመኛ አታዩኝም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 23