ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 21:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

24. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ብትነግሩኝ፣ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤

25. የዮሐንስ ጥምቀት የመጣው ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?”እነርሱም እርስ በርስ በመነጋገር እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው?’ ካልን ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤

26. ‘ከሰዎች ነው’ ካልን ደግሞ፣ ‘ሕዝቡ ዮሐንስን ነቢይ ነው’ ብሎ ስለሚያምን እንፈራለን።”

27. ስለዚህ፣ “አናውቅም” ብለው ለኢየሱስ መለሱለት።እርሱም፣ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

28. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለው።

29. “ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለው፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ።

30. “ወደ ሁለተኛው ልጁ ሄዶ እንደዚያው አለው፤ ልጁም ‘እሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለው፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ።

31. “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?”እነርሱም፣ “የመጀመሪያው ልጅ” አሉት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል፤

32. መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።

33. “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ አጥር አጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 21