ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 21:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤

2. እንዲህ አላቸው “ባቅራቢያችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው።

3. ማንም ሰው ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት፤ ወዲያውኑ ይሰዳቸዋል።”

4. ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።

5. “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣በአህያዪቱና በግልገሏ፣በውርንጫዪቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ”

6. ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።

7. አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው።

8. ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን፣ በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ጣል ጣል አደረጉ።

9. ቀድሞት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፣“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤”“በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤”“ሆሣዕና በአርያም!”

10. ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች።

11. ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ።

12. ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን አባረራቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣

13. “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን፣ ‘የዘራፊዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው።

14. በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው።

15. ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ።

16. እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ” አሉት።ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 21