ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 20:14-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ።

15. ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኝነት ያዘህን?’

16. “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”

17. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤

18. “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለኦሪት ሕግ መምህራን አልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም እንዲሞት ይፈርዱበታል፤

19. እንዲያላግጡበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።”

20. ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።

21. እርሱም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት።እርሷም፣ “እነዚህ ሁለት ልጆቼ፣ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ ፍቀድ” አለችው።

22. ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን?” አላቸው።እነርሱም፣ “እንችላለን” አሉት።

23. እርሱም፣ “ከጽዋዬ በርግጥ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜና በግራዬ መቀመጥ አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምፈቅደው ነገር አይደለም” አላቸው።

24. ዐሥሩም ይህንን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለቱን ወንድማማቾች ተቈጧቸው።

25. ኢየሱስም አንድ ላይ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለ ሥልጣኖቻቸውም በኀይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ፤

26. በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ትልቅ መሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ ይሁን፤

27. የበላይ ለመሆን የሚሻም የእናንተ የበታች ይሁን፤

28. የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአልና።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 20