ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 2:16-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ።

17. በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤

18. “የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምጽ፣በራማ ተሰማ፤ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤መጽናናትም አልቻለችም፤ልጆቿ ሁሉ አልቀዋልና።”

19. ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣

20. “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው።

21. ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤

22. ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤

23. ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 2