ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 19:5-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን?

6. ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”

7. እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍቺውን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት።

8. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤

9. እላችኋለሁ፤ በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፣ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።”

10. ደቀ መዛሙርቱም፣ “የባልና የሚስት ጒዳይ እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል” አሉት።

11. ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ከተሰጣቸው በስተቀር ይህንን ትምህርት ማንም ሊቀበል አይችልም፤

12. ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”

13. ከዚያም እጆቹን በላያቸው ላይ ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አቀረቧቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡትን ሰዎች ገሠጿቸው።

14. ኢየሱስም፣ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማይ እንደ እነርሱ ላሉት ናትና” አላቸው።

15. እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ።

16. ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት አገኝ ዘንድ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው።

17. ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዛቱን ጠብቅ” አለው።

18. ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዛት?” ሲል ጠየቀ።ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 19