ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 19:21-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ፣ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም ሀብት ታገኛለህ። ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

22. ጐልማሳው ሰውየም ይህን ሲሰማ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ።

23. ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው።

24. ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።”

25. ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ።

26. ኢየሱስም እየተመለከታቸው፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።

27. ጴጥሮስም መልሶ፣ “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው።

28. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም የተከተላችሁኝ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ።

29. ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን ፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።

30. ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ብዙ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 19