ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 19:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”

13. ከዚያም እጆቹን በላያቸው ላይ ጭኖ እንዲጸልይላቸው ሕፃናትን ወደ እርሱ አቀረቧቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ሕፃናቱን ያመጡትን ሰዎች ገሠጿቸው።

14. ኢየሱስም፣ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማይ እንደ እነርሱ ላሉት ናትና” አላቸው።

15. እጁንም ከጫነባቸው በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነሥቶ ሄደ።

16. ከዚያም አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት አገኝ ዘንድ ምን መልካም ነገር ልሥራ” ሲል ጠየቀው።

17. ኢየሱስም፣ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንዱ ብቻ ነው፤ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለግህ ግን ትእዛዛቱን ጠብቅ” አለው።

18. ሰውየውም፣ “የትኞቹን ትእዛዛት?” ሲል ጠየቀ።ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤

19. አባትህንና እናትህን አክብር፤ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።”

20. ጐልማሳውም ሰውየ፣ “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” አለው።

21. ኢየሱስም፣ “ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ፣ ሄደህ ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ፣ ገንዘቡን ለድኾች ስጥ፤ በሰማይም ሀብት ታገኛለህ። ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

22. ጐልማሳው ሰውየም ይህን ሲሰማ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እያዘነ ሄደ።

23. ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው።

24. ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።”

25. ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ።

26. ኢየሱስም እየተመለከታቸው፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 19