ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 16:2-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ምሽት ላይ፣ ‘ሰማዩ ስለ ቀላ ብራ ይሆናል’ ትላላችሁ፤

3. ንጋት ላይም፣ ‘ሰማዩ ቀልቶአል፣ ከብዶአልም፤ ስለዚህ ዝናብ ይዘንባል’ ትላላችሁ። የሰማዩን ገጽታ ትለያላችሁ፤ ነገር ግን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉም።

4. ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።” ከዚያም ኢየሱስ ትቶአቸው ሄደ።

5. ባሕሩን እንደ ተሻገሩም፣ ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ረስተው ነበር።

6. ኢየሱስም፣ “ልብ በሉ፤ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠበቁ” አላቸው።

7. እነርሱ ግን እርስ በርሳቸው፣ “እንጀራ ስላልያዝን ይሆናል” ተባባሉ።

8. ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ እንጀራ ስለ አለመያዛችሁ ለምን ትነጋገራላችሁ?

9. አምስቱ እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ አታስታውሱምን?

10. እንዲሁም ሰባቱ እንጀራ ለአራት ሺህ ሰው በቅቶ ስንት መሶብ ተርፎ እንዳነሣችሁ ልብ አላላችሁም ማለት ነውን?

11. ታዲያ የነገርኋችሁ ስለ እንጀራ እንዳልሆነ እንዴት አታስተውሉም? አሁንም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ።”

12. በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን፣ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው።

13. ኢየሱስ ፊልጶስ ቂሣርያ ወደተባለው አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለመሆኑ ሰዎች፣ የሰውን ልጅ ማን ነው ይላሉ?” ብሎ ጠየቃቸው።

14. እነርሱም፣ “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት።

15. እርሱም፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው።

16. ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ።

17. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ብፁዕ ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም አይደለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 16