ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 15:31-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደህና ሲሆን፣ አንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ።

32. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለሆናቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ በራብ ዝለው እንዳይወድቁ ጦማቸውን ልሰዳቸው አልፈቅድም” አለ።

33. ደቀ መዛሙርቱም፣ “በዚህ ምንም በሌለበት ምድረ በዳ ይህንን ሁሉ ሕዝብ ለማብላት በቂ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት።

34. ኢየሱስም፣ “ለመሆኑ ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣ” አሉት።

35. እርሱም ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤

36. ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ።

37. ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ።

38. የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።

39. ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ በጀልባ ወደ መጌዶል ሄደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 15