ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 14:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሄሮድስ የልደቱን ቀን ሲያከብር፣ የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈን ደስ ስላሰኘችው፣

7. የምትጠይቀውን ሁሉ ሊሰጣት በመሓላ ቃል ገባላት።

8. ልጅቷም በእናቷ ተመክራ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን ላይ አድርገህ አሁኑኑ ስጠኝ” አለችው።

9. በዚህ ጊዜ ንጉሡ አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ጥያቄዋ እንዲፈጸምላት አዘዘ።

10. ልኮም በወህኒ ውስጥ እንዳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠ።

11. የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን ላይ አድርገው ለልጅቱ ሰጧት፤ ልጅቱም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች።

12. የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም ሄደው የሆነውን ለኢየሱስ ነገሩት።

13. ኢየሱስ የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ከነበረበት ተነሥቶ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ሰምተው፣ ከየከተማው በእግር ተከተሉት።

14. ኢየሱስም ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ አይቶ ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው።

15. እየመሸ በመሄዱም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ ስፍራ ምንም የማይገኝበት ምድረ በዳ ነው፤ ጊዜው እየመሸ ስለ ሆነ፣ ወደ መንደሮች ሄደው የሚበሉት ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት።

16. ኢየሱስ ግን፣ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ የሚበሉትን እናንተ ስጧቸው” አላቸው።

17. እነርሱም፣ “በዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት።

18. እርሱም፣ “እስቲ ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው።

19. ከዚያም ሕዝቡ በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ዓይኑን ወደ ሰማይ በማቅናት አመስግኖና ባርኮ እንጀራውን ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ ሰጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 14