ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 14:25-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት መጣ።

26. ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲመጣ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ምትሀት ነው!” በማለት በፍርሃት ጮኹ።

27. ኢየሱስም ወዲያውኑ፣ “አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ አትፍሩ” አላቸው።

28. ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ከሆንህስ፣ በውሃው ላይ እየተራመድሁ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው።

29. እርሱም፣ “ና” አለው።ጴጥሮስም፣ ከጀልባው ወርዶ በውሃው እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ።

30. ነገር ግን የነፋሱን ኀይል ባየ ጊዜ ፈራ፤ መስጠምም ሲጀምር፣ “ጌታ ሆይ፤ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ።

31. ኢየሱስም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፣ “አንተ እምነት የጐደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው።

32. ኢየሱስና ጴጥሮስ ጀልባው ላይ እንደ ወጡ ነፋሱ ጸጥ አለ።

33. ከዚያም በጀልባው ውስጥ የነበሩት፣ “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።

34. ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ጌንሴሬጥ ወደተባለ ቦታ ደረሱ።

35. ነዋሪዎቹም ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ፣ በዙሪያው ወዳለ አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ የታመሙትን ሁሉ ወደ እርሱ በማስመጣት፣

36. በሽተኞቹ የልብሱን ጫፍ ብቻ ይነኩ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 14