ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 14:19-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ከዚያም ሕዝቡ በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ዓይኑን ወደ ሰማይ በማቅናት አመስግኖና ባርኮ እንጀራውን ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ ሰጡ።

20. ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።

21. የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።

22. ወዲያውኑ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት አዘዛቸውና እርሱ ሕዝቡን ለማሰናበት ወደ ኋላ ቀረት አለ።

23. ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በጨለመም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር፤

24. በዚያ ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩን ዘልቃ እየተጓዘች ሳለች ነፋስ ተነሥቶ በማዕበል ትንገላታ ጀመር።

25. ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት መጣ።

26. ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲመጣ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ምትሀት ነው!” በማለት በፍርሃት ጮኹ።

27. ኢየሱስም ወዲያውኑ፣ “አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ አትፍሩ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 14