ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 12:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር።

2. ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን መደረግ የሌለበትን እያደረጉ ነው” አሉት።

3. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን?

4. ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባ፤ ለካህናት እንጂ ለእርሱም ሆነ አብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት በላ።

5. ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም?

6. ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ።

7. ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።

8. የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”

9. ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤

10. በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዶአል?” ብለው ጠየቁት።

11. እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጎትቶ አያወጣውምን?

12. ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 12