ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ቀጥሎም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል ስትመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” አላቸው።

የኢየሱስ መልክ አበራ

2. ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ይዞአቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤

3. ልብሱም በምድር ላይ ማንም አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ።

4. ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

5. ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው።

6. እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር።

7. ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ።

8. ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሮአቸው አልነበረም።

9. ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።

10. እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።

11. ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት።

12. ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል?

13. ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።”

ርኩስ መንፈስ ያለበት ልጅ ተፈወሰ

14. ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው፣ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ።

15. ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ።

16. እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጒዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው።

17. ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤

18. በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።”

19. ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው።

20. ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም አረፋ ይደፍቅ ጀመር።

21. ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤

22. ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።”

23. ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው።

24. ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ።

25. ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው።

26. ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቶአል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ።

27. ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ።

28. ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

29. እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው።

30. ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤

31. ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር።

32. እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?

33. ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው።

34. እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ።

35. ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው።

36. ትንሽ ልጅ አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ አቅፎትም፣

37. “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው።

የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው

38. ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፣ እኛን ስለ ማይከተልም ከለከልነው” አለው።

39. ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤

40. የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና፤

41. እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም።”

ለሌላው መሰናክል መሆን

42. “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።

43. ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጒንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤

44. በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።

45. እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤

46. በገሃነም ትሉ አይሞትም እሳቱ አይጠፋምና።

47. ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጒለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤

48. “በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና፤

49. ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና።

50. “ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”