ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 6:43-56 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

43. ደቀ መዛሙርቱም ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።

44. እንጀራውንም የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ።

45. ወዲያውም እርሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቤተ ሳይዳ ቀድመውት እንዲሻገሩ አዘዛቸው፤

46. ከዚያም ትቶአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።

47. በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር።

48. ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር።

49. ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሎአቸው ጮኹ፤

50. ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።

51. እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሮአቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤

52. የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር።

53. በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ።

54. ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤

55. ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር።

56. በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 6