ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

2. ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች፣ ተደነቁ።እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ!

3. ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት።

4. ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በቤተ ሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው።

5. እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤

6. ባለማመናቸውም ተደነቀ።ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።

7. ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው።

8. ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤

9. ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤

10. ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 6