ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 4:28-41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤

29. ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ አጨዳ ይጀምራል።”

30. ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን?

31. በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤

32. ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትላልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”

33. ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው።

34. ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነ ግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።

35. ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው።

36. እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ።

37. በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር።

38. ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?” አሉት።

39. እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ “ጸጥ፣ ረጭ በል!” አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ።

40. ደቀ መዛሙርቱንም፣ “ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?” አላቸው።

41. እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 4