ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 4:12-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ይኸውም፣ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣ መስማቱን እንዲሰሙ ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።”

13. ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ?

14. ዘሪው ቃሉን ይዘራል።

15. አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል።

16. እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ ቦታ ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤

17. ነገር ግን ሥር የሌላቸው ስለሆኑ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ።

18. ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤

19. ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን አንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳ ያፈራ ያደርጉታል።

20. ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ሥልሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

21. እንዲህም አላቸው፤ “መብራት አምጥታችሁ ከዕንቅብ ወይም ከዐልጋ ሥር ታስቀምጣላችሁን? የምታስቀምጡት በመቅረዙ ላይ አይደለምን?

22. ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤

23. ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”

24. በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል።

25. ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 4