ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 16:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ።

2. በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጠዋት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣

3. “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።

4. ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባሎ አዩ።

5. ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ።

6. እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የምትፈልጉት የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው፤ እርሱ ተነሥቶአል፤ እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ።

7. ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።”

8. ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም።

9. በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት በመጀመሪያ ታየ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 16