ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 15:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር።

11. የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ።

12. ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

13. እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።

14. ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው።እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ።

15. ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

16. ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደተባለ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ።

17. ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት።

18. ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤

19. ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት።

20. ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

21. የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 15