ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 14:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤

8. እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች።

9. እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”

10. ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።

11. እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር።

12. የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።

13. እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤

14. ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሎአል በሉት፤

15. እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።”

16. ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ።

17. በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።

18. በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 14