ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 14:61-72 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

61. ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው።

62. ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ።

63. ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል?

64. ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ፣ ምን ይመስላችኋል?”፤እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት።

65. በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

66. ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤

67. ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣“አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

68. እርሱ ግን፣ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ አለ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ።

69. ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፣ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደ ገና ተናገረች።

70. እርሱ ግን አሁንም ካደ።ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፣ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፣ በእርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት።

71. እርሱ ግን፣ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር።

72. ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። ጴጥሮስም፣ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 14