ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 14:29-44 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ።

30. ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፣ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።

31. ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።

32. ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው።

33. ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር።

34. ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።

35. ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፣

36. “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ።

37. ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፣ “ስምዖን ሆይ፣ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ?

38. ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

39. እንደ ገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው።

40. ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር።

41. ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደ ተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል! ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።

42. ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቶአል።”

43. ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፣ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሓፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ።

44. አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 14