ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 13:21-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው’ ቢላችሁ አትመኑ።

22. ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ።

23. ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ።

24. “በዚያን ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤

25. ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’

26. “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል።

27. እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል።

28. “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤

29. እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ።

30. እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤

31. ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።

32. “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም።

33. ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም።

34. ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል።

35. እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤

36. ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 13