ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 12:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች።

23. እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት።

24. ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ነው!

25. ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም።

26. ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን?

27. እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል።”

28. ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።

29. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤

30. አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’

31. ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።”

32. ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤

33. እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”

34. ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።

35. ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ?

36. ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ጌታ ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው።” ይላል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 12