ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 10:41-51 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

41. ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ።

42. ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤

43. በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤

44. ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤

45. የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”

46. ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

47. እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።

48. ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።

49. ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው።እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት።

50. እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፣ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ።

51. ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው።ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 10