ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 10:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።

2. አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።

3. እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው።

4. እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዶአል” አሉ።

5. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው።

6. ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።

7. ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤

8. ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤

9. ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየው።”

10. እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት።

11. እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤

12. እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።

13. ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።

14. ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።

15. እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 10