ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 1:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር።

9. በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ።

10. ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤

11. “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።

12. ወዲያውም መንፈስ ቅዱስ ወደ በረሓ መራው፤

13. በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በበረሓ ቈየ። ከአራዊትም ጋር ነበር፤ መላእክትም አገለገሉት።

14. ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ ሄዶ፣

15. “ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” እያለ ይሰብክ ነበር።

16. ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፣ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው።

17. ኢየሱስም፣ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።

18. እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት።

19. ትንሽ እልፍ እንዳለ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፣

20. ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም አባታቸውን ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር በጀልባው ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ።

21. ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 1