ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 1:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤

24. “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!”

25. ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው።

26. ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ።

27. ሕዝቡ በሙሉ በመገረም፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው? ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት መሆኑ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ።

28. ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ።

29. ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ።

30. የስምዖን አማት በትኵሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤

31. ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኵሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር።

32. ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ።

33. የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 1