ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 1:21-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ።

22. እንደ ጸሓፍት ሳይሆን፣ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ።

23. በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤

24. “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!”

25. ኢየሱስም፣ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው።

26. ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኀይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ።

27. ሕዝቡ በሙሉ በመገረም፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው? ሥልጣን ያለው አዲስ ትምህርት መሆኑ ነው! ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል!” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ።

28. ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ።

29. ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ።

30. የስምዖን አማት በትኵሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 1