ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 9:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጒዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤

14. ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።”

15. ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ፤ ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤

16. እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።”

17. ሐናንያ ሄዶ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና፣ በመንፈስ ቅዱስም እንድት ሞላ እኔን ልኮኛል” አለው።

18. ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤

19. ምግብም በልቶ በረታ።ሳውል በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋር አያሌ ቀን ተቀመጠ።

20. ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ።

21. የሰሙትም ሁሉ በመገረም፣ ይህ ሰው “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለምን? ደግሞም ወደዚህ የመጣው እነርሱን አስሮ ወደ ካህናት አለቆች ሊወስዳቸው አልነበረምን?” አሉ።

22. ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።

23. ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤

24. እርሱ ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤

25. የእርሱ ተከታዮች ግን በሌሊት በከተማዋ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት።

26. ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋር ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት።

27. ይሁን እንጂ ባርናባስ ወስዶ ወደ ሐዋርያት አመጣው፤ ሳውልም በጒዞው ላይ ሳለ ጌታን እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንዴት እንደ ተናገረው እንዲሁም በደማስቆ የጌታን ስም እንዴት በድፍረት እንደ ሰበከ ነገራቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 9