ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 9:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ” ብሎ ጠራው።እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ።

11. ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥ ተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤

12. ምክንያቱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቶአል።”

13. ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጒዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤

14. ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።”

15. ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ፤ ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤

16. እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።”

17. ሐናንያ ሄዶ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና፣ በመንፈስ ቅዱስም እንድት ሞላ እኔን ልኮኛል” አለው።

18. ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤

19. ምግብም በልቶ በረታ።ሳውል በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋር አያሌ ቀን ተቀመጠ።

20. ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ።

21. የሰሙትም ሁሉ በመገረም፣ ይህ ሰው “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለምን? ደግሞም ወደዚህ የመጣው እነርሱን አስሮ ወደ ካህናት አለቆች ሊወስዳቸው አልነበረምን?” አሉ።

22. ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 9