ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 9:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል አሁንም እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤

2. የጌታን መንገድ የሚከተሉትን ወንዶችንም ሆኑ ሴቶችን በዚያ ካገኘ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ እንዲችል፣ በደማስቆ ለነበሩት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ለመነው።

3. ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፣

4. እርሱም በምድር ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።

5. ሳውልም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?” አለው።እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ።

6. አሁንም ተነሥተህ ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።”

7. ከሳውል ጋር ይጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንንም ባላዩ ጊዜ፣ አፋቸውን ይዘው ቆሙ።

8. ሳውልም ከወደቀበት ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት።

9. ሦስት ቀንም ታወረ፤ እህል ውሃም አልቀመሰም።

10. በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ” ብሎ ጠራው።እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ።

11. ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥ ተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤

12. ምክንያቱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቶአል።”

13. ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጒዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤

14. ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።”

15. ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ፤ ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤

16. እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።”

17. ሐናንያ ሄዶ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና፣ በመንፈስ ቅዱስም እንድት ሞላ እኔን ልኮኛል” አለው።

18. ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 9