ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 8:7-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ርኵሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ተፈወሱ፤

8. ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ።

9. ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር።

10. ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤

11. ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር።

12. ነገር ግን ፊልጶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሰበከላቸውን አምነው በመቀበላቸው ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ፤

13. ራሱ ሲሞን እንኳ ሳይቀር አምኖ ተጠመቀ፤ ፊልጶስንም ተከትሎ ሄደ፤ የሚደረገውን ምልክትና ታላቅ ታምራት አይቶም ተገረመ።

14. በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነርሱ ላኳቸው።

15. እነርሱም ሰማርያ በደረሱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ለሰማርያ ሰዎች ጸለዩላቸው፤

16. ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠምቀው ነበር እንጂ ገና መንፈስ ቅዱስ በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር።

17. ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ እነርሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።

18. ሲሞንም ሐዋርያት እጃቸውን በሚጭኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ አይቶ፣ ገንዘብ አመጣላቸውና እንዲህ አላቸው፤

19. “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ።”

20. ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሃልና፣ አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ!

21. ልብህ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ስላልሆነ፣ አንተ በዚህ አገልግሎት ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ የለህም።

22. አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል፤

23. ምክንያቱም በመራራነት ተሞልተህ፣ በዐመፅ ሰንሰለት ተይዘህ አይሃለሁና።”

24. ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 8