ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 8:28-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።

29. መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።

30. ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው።

31. ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው።

32. ጃንደረባው ያነብ የነበረው የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፤“እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፣እንዲሁ አፉን አልከፈተም።

33. ራሱን በማዋረዱም ፍትሕን ተነፈገ፤ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፣ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?”

34. ጃንደረባውም መልሶ ፊልጶስን፣ “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው፣ ወይስ ስለ ሌላ ሰው? እባክህ ንገረኝ” አለው።

35. ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት።

36. በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው።

37. ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤

38. ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው።

39. ከውሃውም በወጡ ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚህ በኋላ አላየውም፤ ሆኖም ደስ እያለውም ጒዞውን ቀጠለ።

40. ከዚያ በኋላ ግን ፊልጶስ በአዛጦን ታየ፤ ቂሳሪያም እስኪደርስ ድረስ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 8