ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 8:22-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. አሁንም ስለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ወደ ጌታም ጸልይ፤ ምናልባት ይህን የልብህን ሐሳብ ይቅር ይልህ ይሆናል፤

23. ምክንያቱም በመራራነት ተሞልተህ፣ በዐመፅ ሰንሰለት ተይዘህ አይሃለሁና።”

24. ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው።

25. ጴጥሮስና ዮሐንስም የጌታን ቃል ከመሰከሩና ገልጠው ከተናገሩ በኋላ፣ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እየሰበኩ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

26. የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤

27. እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር።

28. ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።

29. መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።

30. ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው።

31. ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው።

32. ጃንደረባው ያነብ የነበረው የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፤“እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፣እንዲሁ አፉን አልከፈተም።

33. ራሱን በማዋረዱም ፍትሕን ተነፈገ፤ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፣ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?”

34. ጃንደረባውም መልሶ ፊልጶስን፣ “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው፣ ወይስ ስለ ሌላ ሰው? እባክህ ንገረኝ” አለው።

35. ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት።

36. በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 8