ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 7:52-59 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

52. ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤

53. በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”

54. በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።

55. እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣

56. “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።

57. በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤

58. ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጒልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።

59. እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ጸለየ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 7