ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 7:44-59 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

44. “እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ ነበረች።

45. አባቶቻችንም ድንኳንዋን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤

46. ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤

47. ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር።

48. “ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤

49. “ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ታዲያ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ?ይላል ጌታ፤ወይንስ ማረፊያ የሚሆነኝ የትኛው ቦታ ነው?

50. ይህን ሁሉ የሠራው እጄ አይደለምን?’

51. “እናንት ልባችሁና ጆሮአችሁ ያልተገረዘ፣ አንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁል ጊዜ ትቃወማላችሁ።

52. ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤

53. በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”

54. በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።

55. እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣

56. “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።

57. በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤

58. ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጒልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።

59. እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ጸለየ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 7