ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 7:35-48 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘ገዥና ፈራጅ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህንን ሙሴ እግዚአብሔር በቊጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው።

36. እርሱም መርቶ ከግብፅ አወጣቸው፤ በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።

37. “የእስራኤልንም ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከመካከላችሁ ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር።

38. እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ።

39. “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ።

40. አሮንንም፣ ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት አብጅልን፤ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና’ አሉት።

41. በዚያን ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም።

42. እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤“ ‘እናንት የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ በነበራችሁ ጊዜ፣መሥዋዕትንና መባን ለእኔ አቀረባችሁልኝን?

43. ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣የሞሎክን ድንኳንና የጣዖታችሁን፣የሬምፉምን ኮከብ ከፍ ከፍ አድርጋችሁ ያዛችሁ።ስለዚህ እኔም እንድትጋዙ አደርጋለሁ፤ ከባቢሎንም ወዲያ እሰዳችኋለሁ።

44. “እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ ነበረች።

45. አባቶቻችንም ድንኳንዋን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤

46. ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤

47. ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር።

48. “ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 7