ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 4:28-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።

29. አሁንም ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው።

30. ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ።”

31. ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።

32. ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም።

33. ሐዋርያትም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኀይል መመስከራቸውን ቀጠሉ፤ በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር።

34. ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣

35. በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር።

36. በቆጵሮስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበረ፤ ሐዋርያትም ‘በርናባስ’ ብለው ጠሩት፤ ትርጒሙም ‘የመጽናናት ልጅ’ ማለት ነው፤

37. እርሱም መሬቱን ሸጦ፣ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 4