ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 4:13-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ሰዎቹም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩም ተገነዘቡ።

14. የተፈወሰውን ሰው እዚያው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ስላዩት የሚናገሩበትን ሰበብ አጡ።

15. ስለዚህ ከሸንጎው እንዲያወጧቸው አዘዙ፤ ከዚያም በአንድነት ተሰብስበው ተመካከሩ፤

16. እንዲህም ተባባሉ፤ “እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? በኢየሩሳሌም የሚኖር ሁሉ በእነርሱ እጅ የተደረገውን ድንቅ ታምር ዐውቆአል፣ ስለዚህ ይህንን ማስተባበል አንችልም፤

17. ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር ከእንግዲህ በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ፣ እነዚህም ሰዎች ዳግመኛ በዚህ ስም ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።”

18. ከጠሯቸውም በኋላ፣ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው።

19. ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤

20. እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።”

21. እንደ ገና ከዛቱባቸው በኋላም ለቀቋቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ስለ ነበር ሊቀጧቸው አልቻሉም፤

22. በዚህ ታምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበርና።

23. ጴጥሮስና ዮሐንስም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ተመልሰው የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው።

24. እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤

25. በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤“ ‘አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ?ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ?

26. የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ገዦችም በአንድነት ተሰበሰቡ፤በጌታ ላይ፣በተቀባውም ላይ ተከማቹ።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 4